You are here

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

ኢትዮጵያውያን እንብላ እንደምንለው ሁሉ እንስራስ ማለት እንወዳለን? አይመስለኝም! አሁን ያለንበት ሁኔታ ምስክር በአካልና በአዕምሮአችን ስለማንሰራ ነው፡፡ ጉድ ፈላ!

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

መሰረታዊ የአስሊ ዕውቀት፡፡ የአስሊ አጠቃቀም አጉል ባህሪ ካለወት አስሊወ በቫይረስና በሰላዮች ይጠቃል፡፡ ርካሽ ወይም ነጻ የሆኑ ጥሩ አማራጮችን ያውቃሉ?

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

ስለ ብቃትዎ ምን ያውቃሉ? ለምሳሌ ስለ እልህና ንዴት፤ ወድቆ መነሳት፤ ነጻነት፤ መምራትና መግባብት ወዘተ፡፡ ማሰብ፣ መናገርና ማድረግ መተው ዝምታ ነው!

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

ስለ ባህሪዎ ምን ያውቃሉ? ቀላል ነገሮች ላይ ይሳሳታሉ? ለምሳሌ በቀጠሮ መዘግየት፣ ቋንቋ መቀላቀል፣ ከማዳመጥ ይልቅ ብዙ ማውራት፣ እምነትዎስ ነካ ነካ ነው?

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

የሚያልሙትን ስራ አግኝተው ለማቆየት ስልቱን ያውቁታል? በስራ አለም ውስጥ የተጻፉና ያልተጻፉ ህጎችን ልብ ካሉ በስራዎ ለመደሰት፣ ለማደግና ለመርካት ይረዱወታል!!

Tatariw Amharic website Ethiopia wake up

በቀላሉ እራስዎን ይንከባከባሉ? የሚበላ ምግብ፣ የሚጠጣ መጠጥና የሚታሰብ ሃሳብ ወደ ሰውነታችን ስለሚገባ ህይወታችን ውስጥ ሚና አለው፡፡ ለምን?

1
2
3
4
5
6

"እንብላ!" እንደምንለው ሁሉ "እንስራ!" ብንል ኖሮ የት እንደርስ ነበር? "ዲያስፖራና የኢትዮጵያ እንጀራ"

tatariw's picture
Submitted by tatariw on Tue, 03/31/2015 - 11:49
Tatariw Ethiopia Amharic addis ababa Ethiopia wake up

ናንት ምን ነበር? ዛሬ ምን ተፈጠረ? ወደፊትስ ምን ሊመጣ ይችላል? ብሎ ማሰብ ትናንት የተከሰተው ለዛሬ ትምህርት እንዲሆነንና ዛሬ የምንሰራው ለነገ መሰረት እንዲሆነን ይረዳናል። በሌላ አይነት አባባል የትናንቱን የረሳ ዛሬ ትምህርት መውሰድ አይችልም። ዛሬ ያልሰራ ደግሞ ለነገ መሰረት ወይም እቅድ ስለሌለው ለውጥ አይመጣም። ከጥቂት ኢትዮጵያውያን በስተቀር ብዙ ዲያስፖራ ኢትዮያዊ በመሰደዱና በመሸሹ ብቻ ነጻ የወጣ ይመስለዋል።

ይህ ጽሁፍ ኢላማው በዲያስፖራና ከኢትዮጵያ በሚመጣ እንጀራ መካከል ስላለው ቁርኝት በመጠኑ ለመግለጽ ነው። እዚህ ላይ እንጀራ ቢጠቀስም ምግብ የሆነ ሁሉ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ቆጮ፣ ቅመማ ቅመምና ቂቤንም ይጨምራል። የባህል ምግባችን የሚጥምና ልዩ ስለሆነ ይናፍቀናል። ሆኖም ግን የባህል ምግባችን ከኢትዮጵያ ባይመጣም ውጭ ሃገር ሆነን የባህል ምግባችንን ለመስራት ምርጫወች አሉን። እነዚህን ምርጫወች የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ እርገጠኛ ነኝ። እንጀራው ውጭ ሃገር ቢሰራም ብዙውን ጊዜ ወጣ-ወጡ ከኢትዮጵያ በመጣ ቅመማ ቅመም ስለሚሰራ ከሁሉም ነገር ነጻ መሆን አይቻልም። ይህን በተመለከተ ስንቶቻችን እንደምናስበው መናገር አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ እኔ እራሴ ወደ ሬስቶራንትም ሆነ ለጉብኝት ስሄድ ያጋጥመኛል። ሰው ፍጹም መሆን ስለማይችል ደግሞ እኔም እራሴ ቃሌን ያፈረስኩበት ጊዜ አለ። በዳቦም ሆነ ውጭ ሃገር በተሰራ እንጀራ ቢበሉት ወጡ ያው ከሆነ ንጹህ መሆን አይቻልም። ሆኖም ግን፤ ለመጥቀስ ያህል በአመት ከ5-7 ጊዜ ውጭ ሃገር በተሰራ እንጀራና ከኢትዮጵያ በመጣ ቅመም በልቻለሁ። ለጉብኝትም ሄጀ ባለፉት 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ጊዚያት ሙሉ በሙሉ አፍርሻለሁ። ወዲያውኑ ምርጫ ስላልነበረኝና ስለበላሁ በጣም ጸጽቶኛል። ለመናዘዝ ካልሆነ በስተቀር ጸጸቴን እዚህ መጥቀስ ዋጋ ቢስ ነው። የባህል ምግባችን ላይ መጨከን ከባድ ነው። ምናልባት ዋናው እንጀራ ስለሆነ አብዛኛው ዲያስፖራ ካመነበት ከኢትዮጵያ የሚመጣውን እንጀራ መጀመሪያ በመተው ቢጀምርና በኋላ ደግሞ ወደ ቅመሞቹ ቢሸጋገር አንዱ አማራጭ ነው።

ከዚህ በታች ያሉት ሊጠየቁ የሚችሉ 12 ጥያቄዎችና ተቀራራቢ መልሶች ናቸው።

1ኛ) ከኢትዮጵያ የሚመጣ እንጀራ መተውና ከመግዛት መቆጠብ ፖለቲካ ነው???
በማንኛውም ስርአት ውስጥ ነጋዴ ስለሚኖር ነጋደወች አሁንም ሆነ ወደፊት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር እንጀራ መሸጣቸው አይቀርም። ስለዚህ ከኢትዮጵያ የመጣ እንጀራ ከመግዛት መቆጠብ ፖለቲካ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ችግር እስካለ ድረስና እርስዎ ያለፉትን/የነበሩበትን ግን ወገንዎ አሁን የሚኖርበት ችግር ስለሆነ እርስዎ ምንም ሳይጎድልብዎት ለመካፈልና ለመርዳት ከፈለጉ የሚወስዱት እርምጃ ነው። ብዙ ሰወች የሚሳሳቱት ውኃ የቀጠነው በፖለቲካ ምክንያት ሲሉ ነው። እርስዎ ግን ጥሩና ትክክል ሃሳባዊ ስራ መስራት አለብወት። የሚወስኑት ውሳኔ ከገንዘብና ከግለሰቦች ጋርም መያያዝ የለበትም። እርስዎ ትልቁን ስዕል ኢትዮጵያን ማየትና ከሚቸግረው ወገንዎ ጋር የአዕምሮ ትስስር ማድረገዎን ነው። ልክ አይነዎን ገርበብ አድርገው ፈጣሪ አምላካን በጸሎት እንዲሚያስቡት ሁሉ ለኢትዮጵያና ለወገንዎ በተግባር ማሰብ ጋር ይመሳሰላል።

2ኛ) ከኢትዮጵያ የመጣ እንጀራ መብላት የኔ ምርጫ ነው!
ከኢትዮጵያ ከመጣ እንጀራ መቆጠብ የግል ምርጫ ነው። ሰው በምርጫው ላለመርዳት ይችላል። ሰው አይቶና ሰምቶ እንዳላየና እንዳልሰማ መሆን ምርጫው ነው። አውቆም እንዳላወቀ መሆን ምርጫው ነው። ህይወታችን በምርጫወች የተሞላች ነች። ምርጫችን ግን ጥሩ ምክንያት ያለውና ህሊናም የማይወቅስ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

3ኛ) እኔ ምን መብላት እንዳለብኝ ማንም ሊወስን አይችልም!
ልክ ነው። ሰው ምን መብላት እንዳለበት በራሱ ነው የሚወስነው። ወገኖቻችን ካለባቸው ችግር አንጻር ግን ከመወሰናችን በፊት "ሃሳባዊ ስራ" ስራ ላይ መስራት ውሳኔአችንን ትክክል ያደርገዋል። እዚሁ ውጭ ሃገር ሁሉም ጥሬ ነገር ስለሚገኝ የባህል ምግብ መስራት እንችላለን። ለምሳሌ በጤፍ ፋንታ ሌላ አይነት ዱቄቶች መጠቀም ይቻላል። ብዙ አይነት ቅመሞችንም መርጦ መግዛት ይቻላል። እንዳውም የተሻለና ጤናማ የባህል ምግብ ውጭ ሃገር መስራት ይችላሉ

4ኛ) ከኢትዮጵያ የመጣ እንጀራ በላሁ አልበላሁ ኢትዮጵያ ላሉ ወገኖቼ ለውጥ አያመጣም!
በተለያየ መልኩ ለውጥ ያመጣል። አረብ ሃገር፣ አውሮጳ፣ አሜሪካ፣ አፍሪቃ፣ አውስትራሊያ ወዘተ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንጀራ፣ እንጀራ ካለ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚወጣው እንጀራ በጣም ብዙ ነው። ስለዚህ ነጋዴወችና ላኪወች የውጭ ገበያ ላይ ስለሚያተኩሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ዋጋ ይወደድባቸዋል። ለዚህ ጥናት ባይካሄድም በየሃገሩ ያለው ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊ የባህል ምግብ በፈለገ ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ሊጨምር ይችላል። ለውጡን ከገንዘብ ጋር ብቻም ማያያዝ የለበወትም። ዋናው ነጥቡ ግን ሁል ጊዜ ሁሉንም ነገር ከገንዘብ ጋር ማያያዝ የለብንም። ለወገኖቻችን ማሰብ መቻላችንንና የምንፈጥረውን የአለሁልህ አዕምሮ ትስስር ነው። አይተንና ሰምተን ችግሩን ማባባስ ሳይሆን ችግሩን መካፈልና ለወገኖቻችን ማሰብ መቻላችን ላይ ነው። የባህል ምግቡን ደግሞ ውጭ ሃገርም ውስጥ መስራት ስለሚቻል አይቀርብንም። በተጨማሪ ለመረዳት የጥያቄ ቁጥር 1ን ምላሽ ይመልከቱ።

5ኛ) ውጭ ሃገር ሬስቶራንት ስላለኝ ኢትዮጵያ ውስጥ እንጀራ ሰርተው የሚልኩትን አስተዳድራለሁ ወይም እየረዳኋቸው ነው!
የቱን ያህል ጠቀም ያለ እርዳታ እንዲሚያደርጉ በዚህ ላይ ብዙ የምለው የለኝም። ሆኖም ግን ነግዴም ውጭ ሃገር ውስጥ ሰርቶ የመሸጥ ምርጫ አለው። ምናልበት ትኩረት ማድረግ ያለብዎት አገልግሎት፣ የምግብ ጥራትና ሰወች ሸተው እንያወጡ የመሳሰሉት ላይ መሆን ያለበት ይመስለኛል። ቆንጆና የሚጥም ምግብ ውጭ ከሰሩ እንዳውም ምግብዎና እርስዎ ዝነኛና ተወዳጅ ይሆናሉ ይመስለኛል። ለሁላችንም ነው እንጂ እርስዎን ለመጉዳት አይደለም። በጣም አዝናለሁ። በተጨማሪ ለመረዳት የጥያቄ ቁጥር 1ን ምላሽ ይመልከቱ።

6ኛ) ኢትዮጵያ ጤፍ ወይም እንጀራ፤ ለምሳሌ ልክ እንደ ቡና ኤክስፖርት ብታደርግ እንዳውም ለኢትዮጵያ ሃገራችን ጥሩ ሊሆን ይችላል።
ምግብና ቡና አንድ አይነት አይደሉም። ለምሳሌ ሰው ምግብ ካልበላ ይርበዋል፤ ቡና ባይጠጣ ግን ሱሱ ያልፍለታል። እንጀራ ወይም እህል ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት ለማድረግ አሁን ጊዜው አይደለም። ምክንያቱም ሰው መሄድ ሳይጀምር መሮጥ አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ ወገኖቻችን በቂ ምግብ ሊኖራቸው ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ እስካነሰ ድረስ ምግብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እንጂ እንዲወጣ አስተዋጾ ማድረግ የለብንም። ቢቻል ኖሮ እንዳውም ከኢትዮጵያ የሚበላ ነገር እንዳይወጣ ጊዚያዊ ህግ ቢኖር ይጠቅመን ነበር።

7ኛ) ከኢትዮጵያ የሚመጣ እንጀራ እወዳለሁ። የሃገሬን ምግብ ልጆቼ እንዲያውቁት እፈልጋለሁ። የባህል ምግባችንን ሌሎች ሃገር ዜጎችም ማስተዋወቅ ይሻላል!
የባህል ምግባችን እይታውና ሲበሉት ልዩ ጣም ስላለው እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን ቀርቶ የውጭ ዜጎችም ይወዱታል። ሆኖም ግን ከላይ እንደተጠቀሰው የባህል ምግቡን ውጭ ሃገርም ቢሆን መስራት ስለሚቻል በመንኛውም መልኩ የባህል ምግባችን አይቀርብንም። ምናልባት ቅምሻው ለየት ሊል ይችላል። ሰው ከፈለገና ደጋግሞ ከሞከረ ማመሳሰል ይችላል። ልጆቹም የባህሉን ምግብ አይረሱትም። አገርቤት ለጉብኝት ሲሄዱ ደግሞ ከፈለጉ እዛም ይበላሉ። ዋናው ነገር ግን ለምን ይህ እንደሚደረግ ወላጆች ለልጆቻቸው ካስረዷቸው ልጆቹም አውቀውት ለወገኖቻቸው እነሱም ማሰብ ይጀምራሉ። ለወደፊትም ከኛ የተሻሉ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል። ማን ያውቃል? ከግልና ከቤተሰ ጥቅም ጋር አጣምሮ ሃገራዊና ወገናዊ አስተሳሰብም ብናዳብር ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል እንጂ አይጎዳትም። የመንፈስና የመተሳሰብ ትስስር በቋሚነት ሊፈጥር የሚችለው አንዱ መንገድ ይኸ ሲሆን ይችላል።

8ኛ) ለምሳሌ ኖርዌይ ውስጥ የሌላ ሃገር ዜጎችም የሃገራቸውን ባህል ምግብ እያስመጡ ሰርተው ይበላሉ። ታዲያ እኔም ልክ እንደነሱ የሃገሬን ምግብ ብበላ ምን ችግር አለው?
የሌሎች ሃገር ዜጎች እንደኛ ተሰርቶ ያለቀ ምግብ በገፍ የሚያስመጡ አይመስለኝም። በጣም ብዙውን ነገር ከውጭ ገዝተው ነው የሚሰሩት ይመስለኛል። በተጨማሪ ደግሞ እኛ ከሌላ ዜጋ ጋር ለመመሳሰል መሞከር የለብንም። ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ መሆን ስላማይችል፤ የራሳችን ምክንያትና ውሳኔ ሊኖረን ይገባል።

9ኛ) ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ችግር ቢኖርም ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ እንደሆነ የሃገሩን ባህል ምግብ ይወዳል። አሁን አንተን ምን አለፋህ?
ይኸ ጥሩ ጥያቄ ነው። እንዴት አድርገንና በየትኛው መንገድ ወገኖቻችንን እንረዳለን የሚለው ጥያቄ እንጂ ሁላችንም መርዳት እንፈልጋለን። መፈለግና ማድረግ ግን ይለያያል። እዚህ ላይ "ሃሳባዊና አካላዊ ስራ" ትኩረት ያስፈልገዋል። ሁሉንም ጽሁፎች አንብበዋቸው ከሆነ ጉዳዩ ስለ "ሃሳባዊና አካላዊ ስራ" ምን ማለት እንደሆነ በቀላሉ የሚያስረዱ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ምግብ እንዲገባ እንጂ ከኢትዮጵያ ምግብ እንዳይወጣ ካደርግን አንዱ የመርጃ መንገድ ነው።

10ኛ) ገንዘብ ወደ ዘመዶቼ ስለምልክ ዘመዶቼ ምግብ ለመግዛት በኢኮኖሚ አይቸገሩም!
ቤተሰብ መርዳት በጣም ጥሩ ነው። ብዙወቻችን ወደ ዘመድ/ቤተሰብ ገንዘብ ስለምንልክ በቀጥታ ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት እንዳለ ያሳያል። ነገር ግን ሁሉም ሰው ውጭ ሃገር ዘመድ የለውም። የጽሁፉ አላማ ግን ዘመድ መርዳታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሰፋ አድርገን እንድናስብ ነው። ለምሳሌ ካደጉ ሃገሮች ውስጥ ኖርዌይን ብንወስድ የሃገሩ ዜጋ የነጻ ህክምና ያገኛል። ስራ ለሌላቸው፣ ደከም ላሉ፣ ለልጆች፣ ለወሊድ ወዘተ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። ይህ ገንዘብ ከሰራተኛው ደመወዝ እየተቆረጠ ለምሳሌ ደከም ላሉና በቂ ለሌላቸው የሚሰጠው በተቻለ መጠን ሃገራቸው ውስጥ የተቸገረ ሰው መኖሪያውን እንዲሸፍን ነው። ይህ የሚያሳየው ህዝቡ ተባብሮ ይረዳዳል ማለት ነው። ዘመድና ቤተሰቦቻቸውንም በግል ይረዳሉ።

11ኛ) ከኢትዮጵያ ምን ያህል እንጀራ ወደ ውጭ እንደሚወጣ ስለማይታወቅ አትልፋ!
በጥናት ባይታወቅም ወደ አረብ ሃገር፣ አውሮጳ፣ አሜሪካ፣ አፍሪቃ፣ አውስትራሊያ ወዘተ ከኢትዮጵያ የሚወጣ እንጀራ/ምግብ በጣም ብዙ እንደሚሆን ማወቅ አያስቸግርም። አሁን ብዛቱን የማወቅ ጉዳይ ሳይሆን እርስዎ ከኢትዮጵያ ከሚመጣ እንጀራ መቆጠብ ከቻሉ ለወገንዎ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ነው። በተጨማሪ ለመረዳት የጥያቄ ቁጥር 1ን ምላሽ ይመልከቱ።

12ኛ) እባክህ የሆዴን ነገር አታንሳብኝ!
ከሚበሉት ውስጥ አንዱን ነገር ብቻ ነው ያነሳሁት። ከግል የሆድ ፍጆታዎ በላይ ካሰቡ የተሻለ ሰው እንዲሆኑ ይረዳዎታል። የባህል ምግባችን ሲሰራ፣ ሲቀመጥና ሲንቀሳቀስ ልዩ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በተለይ እንጀራ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሲላክ ለሰዓታትም ሆነ ለቀናት ለተለያዩ ሙቀትና ቅዝቃዜወች ስለሚጋለጥ ለጤንነትዎም ጥሩ ላይሆን ይችላል። እንጀራ በጣም ልዩ ስለሆነ እንኳን ለሚሸጥ ቀርቶ ለግል ፍጆታ እንኳን እቤት ሲዘጋጅና ሲቀመጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ስለዚህ ከኢትዮጵያ የሚመጣ እንጀራና ሆድዎን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ለጤንነትዎም ማሰብ አለብዎት። ምግብ ዛሬ በልተውት ነገ በመጸዳጃ ብቻ ወጥቶ ዝም አይልም። ወደ ሆድ የሚገባ ነገር በበጎም ይሁን በመጥፎ ህይወታችን ላይ ተጽዕኖ አለው። እራስዎንም ለመጠበቅ ሲሉ ሆድዎ ውስጥ ምን እንደሚገባ ጥንቃቄ ማድረጉ ጥሩ ነው። "አይ ተስማምቶኛል" ካሉም በእግሩ የተንቀሳቀሰ ሰው ሁሉ ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም። ከሆድዎ በላይ ማሰብ ከቻሉ ደግሞ የተሻለ ሰው መሆን ጥሩ መንፈስ እየሰጠ ደስተኛ ያደርጋል። አምላክም ይወደዋል ብዬ አምናለሁ። እስከ ዛሬ ድረስ በአፍወና አደባባይ ላይ ተናግረው ብቻዎ ሲሆኑ ግን የሚበሉ ከሆነ ለራስዎ ታማኝ ለመሆን ይሞክሩ። ሰው ይሳሳታል። አንዳንድ ጊዜም አያስችለውም። በደንብ ልብ ሳይሉ ትኩረት ሳይሰጡበት ቀርተው ሊሆንም ይችላል። አሁን ያለፈው አልፏል። ለወደፊቱ ግን 12ቱ ጥያቄና መልሶች ለሚወስኑት ውሳኔ እንደሚረዳዎት ተስፋ አለኝ።

ማጠቃለያና ማሳሰቢያ፤
እዚህ ገጽ ላይ ብቻ ያለውን ጽሁፍ አንብቦ ለመረዳት አስቸገረዎት? ተያያዥ የሆኑ ሌላ ሶስት ጽሁፎች መጀመሪያ ተጽፈዋል። እነሱን እዚህ ያገኟቸዋል!!
እዚህ ድረስ ስላነበቡ አመሰግናለሁ!!

በተረፈ የዚህን ጽሁፍ ዋና አላማ ለመረዳት "ሃሳባዊና አካላዊ ስራ" ምን እንደሆነ የሚያስረዱ ጽሁፎችን አሉ።

Comments

ሳምሶን's picture

በተግባር ሊተረጎሙ የማይችሉ ብዙ ጥሩ ሃሳቦች አሉ። ከነዛ ውስጥ አንዱ ይሄ ይመስለኛል። በተግባር ሊተረጎም እስካልቻለ ድረስ ጥሩ መሆኑ በራሱ የሚሰጠው ጥቅም የለም። አሳቢውን ጥሩ አሰብክ ሊያስብል ይችል ይሆናል።ለተግባራዊነታቸው የያንዳንዱን ዜጋ GOOD WILL ግድ የሚሉ ውጥኖችን እውን ለማድረግ አስቸጋሪ ነው። አንድን ነገር ሁሉም እንዲያከብረውና እንዲተገብረው አንድም ገዛች መንፈሳዊ አባት አልያም ህግ አስፈጻሚ ሃይል ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ የምናስባቸው ጥሩ ሃሳቦች ብዙ ግዜ ከሃሳብ ቆጥ ወርደው መሬት ላይ ሲራመዱ አይታዩም፡፤ ከሃሳብነት ቆጥ ካልወረደ ደግሞ ሃሳብ ሳይሆን "መልካም ምኞጥ" ነው።

በደንብ ልብ ብለዋል! ይህን ሃሳብ በተግባር ለመተርጎም የእያንዳንዳችን ሙሉና መልካም ፍላጎት ይፈልጋል። ትክክል ነው ብዬ የማምንበትን ሃሳብ ከመጻፍ በስተቀር ለማስፈጸም አቅምም ሆነ አጋጣሚ የለኝም። ሆኖም ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ እንደ ሰው ልጅ ርህራሄ የተላበሰ አስተሳሰብና ህሊና ቢኖረው ኖሮ መጻፍም ሆነ መንገር አያስፈልግም ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ችግር አለ። ይህን እናያለን እንሰማለን። ሰው እንደመሆናችን መጠን ያለ ምንም ገዛችና ህግ አስፈጻሚ በራሳችን አስበን ለወገኖቻችን እርህራሄና የአዕምሮ ትስስር ባደረግን ነበር። በሚታየውና በሚሰማው ችግር ምክንያት እያንዳንዱ ሰው ለወገኑ በራሱ ህሊና መነሳሳት በቻለ ነበር። ይህ በራሱ የሚመጣ ርህራሄ ሰወች ከሌላቸው ግን ልክ እርስዎ እንዳሉት ገዛች መንፈሳዊ አባት አልያም ህግ አስፈጻሚ ሃይል ያስፈልጋል። እንደገና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ተሰሚነት ያላቸው ክፍሎች/ሃይሎች ርህራሄና ህሊና ካላቸው ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ተሰሚነት ያላቸው ክፍሎች/ሃይሎች አደባባይ ላይ ለመናገር ሃሳቡን ይፈሩታል ወይም የሚራራ ልባቸውን አያዳምጡትም። ወይም ሃሳቡን አያምኑበትም። ምክንያቱም እራሳቸውም ተጠቃሚ ወይም የፍጆታው ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ።

የርስዎ ነጥብ ግን ገብቶኛል። ጥሩ ሃሳብ ተግባር ላይ ካልዋለ ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል። ምናልባት በጣት የሚቆጠሩ ሰወች ተግባር ላይ ቢያውሉትም በባህር ላይ ጠብታ እንደሚባለው ይሆናል። በግለሰብ ደረጃ ቢሆንም በየትኛውም ጊዜ ጥሩ ሃሳቦች ተጽፈው ለእርማትም ሆነ ለትችት መቅረብ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። እውነት ነው፤ አንዳንድ አስፈጻሚና ተባባሪ ያጡ ሃሳቦች የምኞት ወይም የህልም ሃሳቦች መስለው ሊታዩ ይችላሉ።

ለአስተያየትዎ በጣም አመሰግናለሁ!! ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የተለየ ዘዴ ወይም ተጨማሪ አስተያየት ካለዎት ይለግሱ። ወይም fantaw አት gmail ዶት com ብለው ከጻፉ መልክትዎ ይደርሰኛል። ከሰላምታ ጋር። //ፋንታው

መለሰ አብርሐም's picture

አባባሉ ተክክለኛ ነው። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም እንኩን "ከሥራ ከምግብ ይታገዛል" የሚባለው። በሥራ ስዓትና ብዙውን ጊዜያቸውን በእዬ መጠጥ ቤቱ የሚጠፉትን የተቀደሰ ስዓት በሥራ ላይ ቢያዉሉት ሀገራችን የት በደረሰች ነበር? በበለጸጉት ሀገሮች በአንድ ቀን ውስጥ ትርፍ ስዓታቸውን የሚጠቀሙበት ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት ነው። ይህ አባባል ከዚህ ጉዳይ ጋ የተያያዘ በመሆኑ ታታሪው ከልቤ አመሰግነዎታለሁ። መለሰ አብርሐም

እኔም አመሰግናለሁ!
ሰው ከሰራና እርስ በእርስ ከተሳሰበ የሚበላው አያጣም ወይም አያንሰውም። //ፋንታው

አዲስ አስተያየት ይጨምሩ